ሕክምናHikimna · Amharic health reference
በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው። Written by an MD. Educational only.
3

ሪህ (ጋውት)

Gout

በሐኪም (MD) የተጻፈ · Written by an MD · 2026-09-21

ምንድን ነው?

ሪህ፣ ጋውት (gout) ተብሎም የሚጠራው፣ ድንገተኛና ከባድ የመገጣጠሚያ ብግነት ነው። ብዙ ጊዜ በእግር አውራ ጣት ይጀምራል፤ ግን ሌሎች ጆይንቶችንም (joints) ሊይዝ ይችላል።

ዩሪክ አሲድ (uric acid) ሲበዛ፣ ክሪስታሎች ተፈጥረው የሰውነትን መከላከያ ምላሽ ያነሳሳሉ። ይህም እብጠትና ሕመም ያመጣል። ምግብ ብቻ ምክንያቱ አይደለም፤ የቤተሰብ ታሪክ፣ የኩላሊት ሁኔታና አንዳንድ መድኃኒቶችም ተጽዕኖ አላቸው። MedlinePlus።

አደገኛ ምልክቶች

ከሚከተሉት አንዱ ካለ ወዲያውኑ እርዳታ ይፈልጉ፦

  • የሞቀና ያበጠ ጆይንት ከትኩሳት ወይም ከብርድ ብርድ ስሜት ጋር።
  • ድንገተኛ የጆይንት እብጠት፣ እየጨመረ የሚሄድ ሕመምና በአጠቃላይ መታመም።

የጆይንት ኢንፌክሽን (joint infection) ሊሆን ይችላል፤ ሪህ ነው ብለው አይጠብቁ። NHS።

ቤት ውስጥ ምን ማድረግ?

  • የሚያምዎትን እግር ወይም እጅ ያሳርፉና ከፍ ያድርጉ። በጆይንቱ ላይ ጫና አይጨምሩ።
  • በፎጣ የተጠቀለለ ቀዝቃዛ ጭምቅ ሊያስታግስ ይችላል፤ በረዶን በቀጥታ በቆዳ ላይ አያድርጉ።
  • በቂ ውሃ ይጠጡ፤ ሐኪም የፈሳሽ ገደብ ከሰጠዎት ግን ያንን ይከተሉ።
  • ለሕመም ጊዜ የታዘዘዎትን ሕክምና ይከተሉ። የሌላ ሰውን መድኃኒት አይውሰዱ።
  • አሎፑሪኖል (allopurinol) ወይም ሌላ ዩሪክ አሲድ የሚቀንስ መድኃኒት ከታዘዘልዎ፣ ሕመሙ ስለጠፋ ብቻ አያቁሙት፤ የሐኪምዎን ዕቅድ ይከተሉ።
ምልክቶች
  • በአንድ ጆይንት ድንገት የሚጀምር ከባድ ሕመም።
  • መሞቅ፣ እብጠትና የቆዳ ቀለም መቀየር።
  • ቀላል ንክኪ፣ ብርድ ልብስ እንኳን፣ መታገስ አለመቻል።
  • ሕመሙ ከጠፋ በኋላ ወራት ቆይቶ መመለስ።
ሐኪም መቼ ማየት?
  • ይህ ዓይነት ሕመም ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጣ፣ ምክንያቱን ያስመርምሩ።
  • ሕመሙ ከተደጋገመ ወይም የታዘዘው ሕክምና ካልረዳ።
  • የዩሪክ አሲድ የደም ምርመራ ሊረዳ ይችላል፤ ግን ምርመራው ብቻውን ሁሉንም አያረጋግጥም። አንዳንዴ የጆይንት ፈሳሽ ምርመራ ያስፈልጋል። NHS።
መከላከያ
  • አልኮልንና ብዙ ስኳር ያላቸውን መጠጦች ይቀንሱ።
  • ለእርስዎ ስለሚስማማ አመጋገብ፣ የሥጋና የጉበት መጠንን ጨምሮ፣ ይወያዩ።
  • የውሃ እጥረትን ይከላከሉ፤ በሚችሉት መጠን ይንቀሳቀሱ።
  • የረጅም ጊዜ ሕክምናና የደም ምርመራ ክትትልን ይቀጥሉ። የአመጋገብ ለውጥ ብቻ ለሁሉም ሰው በቂ አይሆንም።
ለሐኪምዎ የሚጠይቋቸው
  • የጆይንቴ ሕመም ሪህ መሆኑ እንዴት ይረጋገጣል?
  • ለሕመም ጊዜና ለረጅም ጊዜ መከላከያ የሚሆነው ዕቅድ ምንድን ነው?
  • የኩላሊቴ ሁኔታ ወይም መድኃኒቶቼ ሕክምናውን ይቀይራሉ?
ምንጮች

ጥያቄዎችና መልሶች · 3

jimm

እኔ ከ ወገብበታች ወየዉ በጣም ይጠዘጥዘኛል ለእንቅልፍ ሲሄድ እናም እንቅልፍ ቶሎ አይመጣም ጥዝጠዜውን እያሰብኩ 🥺

ሕክምና

ይህ ከሪህ የተለየ ይመስላል፣ ሪህ ብዙ ጊዜ አንድ ጆይንት ላይ ነው የሚያብጠው። ጥዝጣዜው ሲያርፉ የሚብስና እግርዎን ሲያንቀሳቅሱ የሚቀል ነው? እንደዚያ ከሆነ ሬስትለስ ሌግስ ሊሆን ይችላል፣ ብዙ ጊዜ ከአይረን ማነስ ጋር ይያያዛል። ወይስ ከወገብ ወደ አንድ እግር የሚወርድ ህመም ነው?

theb

ሪህ ያለበት ሰው ኢንተርሚተንት ጻም መጾም አለበት?

ሕክምና

ሪህ ያለበት ሰው መጾም ይችላል፣ ግን ረጅም ጾም ዩሪክ አሲድን ለጊዜው ከፍ ስለሚያደርግ ህመሙን ሊቀሰቅስ ይችላል። እንደ 12 ወይም 14 ሰዓት ያለ አጭር ጾም ከብዙ ውሃ ጋር ቢሆን ይቀላል። ክብደት ቀስ ብሎ መቀነስ ሪህን ይረዳል፣ በፍጥነት መቀነስ ግን ያባብሰዋል።

mule

why you mentioned dispora

ሕክምና

Diet changes in the diaspora, like eating more meat or beer, make gout very common. We wanted to make sure the info reaches everyone 😅

ጥያቄዎ ከታየ በኋላ እዚህ ይወጣል። · Your question appears after it is checked.

ተያያዥ ርዕሶች

በሐኪም (MD) የተጻፈ። ለትምህርት ብቻ ነው፤ የግል የሕክምና ምክር አይደለም። ድንገተኛ ችግር ካለ 911 (አሜሪካ) ወይም 907 (አዲስ አበባ)።
ሁሉም ጽሑፎች · ስለ እኛ · ያግኙን